የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማገዝ እና ለዜጎች ይበልጥ ተደረሽ፣ ቀልጣፋ እና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል በዲጂታል የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት በኢትዮ ቴሌኮም እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል ተፈጽሟል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም አስተማማኝ እና ደረጃውን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ /ICT/ መሰረተ-ልማት ማለትም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የመጠባበቂያ ኔትወርክ እና የኔትወርክ ደህንነት ያለው ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል (Modular data center)፣ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል (Network Operation Center)  የዋይድ ኤሪያ እና ሎካል ኤሪያ ኔትወርክ ግንባታ እንዲሁም የሶፍትዌር ደረጃ ዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ማስተዳደሪያ (SD-WAN) ዓለም አቀፍ ደረጃውን እና ጥራቱን ጠብቆ በመገንባት የሚያስረክብ ሲሆን ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢ-ኮርት ሲስተም አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች የትብብር ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ሥልጠና፣ የእዉቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡

የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ፣ አስተማማኝ፣ ተደራሽ፣ ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ጊዜ እና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ግልጸኝነት ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በሌላ በኩል የዚህ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ መጠናቀቅ ዜጎች የፍርድ ቤት ጉዳይ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ፣ የመረጃዎቻቸው ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን፣ ግልጽ የሆነ የፍትሕ አሰራር እንዲሰፍን፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ መረጃዎችን ለመመርመር፣ ውጤታማ እና ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለማግኘት እና የመሳሰሉ ጠቀሜታዎች ይኖረዋል፡፡

በቀጣይም ኩባንያችን በሊድ የዕድገት ስትራቴጂው መሠረት ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር እያከናወነው የሚገኘውን ሠፊ የዲጂታላይዜሽን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ማደረጉን እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

 

 

መጋቢት 26 ቀን 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives