ኩባንያችን በሀገራችን ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን ለማመቻቸት ታስቦ የተጀመረው ቴሌብር፣ ሁለት አመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ 30 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቶ ፈጣን ቀላልና ምቹ በሆነው አገልግሎቱ የማህበረሰባችንን የዲጂታል ህይወት በማቅለል ላይ ይገኛል፡፡
ቴሌብር ባለፉት 22 ወራት ብቻ ከ101 ሺ በላይ ወኪሎች፣ ከ28 ሺህ ነጋዴዎች እንዲሁም ከ19 ባንኮች ጋር ትስስርን የፈጠረ ሲሆን ከ44 አገራት ከ1.95 ሚሊዮን ገቢ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ባስጀመረው የዲጂታል ፋይናንስ የብድርና የቁጠባ አገልግሎቱ በቴሌብር መላ የብድር አገልግሎት ለ1.4 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹ 2.1 ቢሊዮን ብር ያበደረ ሲሆን 400 ሺ የቴሌብር ሳንዱቅ የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ 1.7 ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩልም ከበርካታ የግል እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን የቴሌብርን የጅምላ ክፍያ ዘዴ በመጠቀም እንደ ደመወዝ ያሉ የጅምላ ክፍያዎች ማስተናገድ፣ የትራፊክ ቅጣት ክፍያዎችን፣ እንደ ብሄራዊ የነዳጅ ድጎማ ያሉ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር እንዲያደርጉ አስችሏል፡፡
ቴሌብር ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶቹን በማስቀጠል በየጊዜው እያደገ የመጣውን የዲጂታል ፍላጎት ለማርካትና የዲጂታል የኑሮ ዘይቤን ለማሳለጥ፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በአንድ አካቶ ደንበኞች ከቴሌብር መተግበሪያቸው ላይ ሆነው ሌሎች የተለያዩ መተግበሪያዎችን መጠቀም ወደሚችሉበትና “በአንድ መተግበሪያ እልፍ ጉዳይ” ወደሚያከናውኑበት ቴሌብር ሱፐርአፕ ወደተሰኘ መተግበሪያ በልጽጎ ዛሬም የደንበኞቹን ተሞክሮ ይበልጥ ሊያልቅ ቀርቧል፡፡
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ቴሌብር ሱፐርአፕ (telebirr Supper App) በዕለት ተዕለት ኑሯቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞችንና አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ ታግዘው ለደንበኞች ለማድረስ የሚሰሩ ቢዝነሶችን ለማገዝና ለማሳለጥ ታስቦ የበለጸገ መተግበሪያ ሲሆን እንደ የቴሌብር የፋይናንሻል አገልግሎት፣ ኢ-ኮሜርስ እና አነስተኛ መተግበሪያዎችን (mini-Apps) እንዲሁም ሶሻል ኔትዎርኪንግ እና የህይወት ዘይቤ (Social networking & Lifestyle) የመሳሰሉ አገልግሎቶችን በማቅረብ ደንበኞች በአንድ ጊዜ ፈርጀብዙ የዲጂታል ግብይት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም ለማንኛውም የግዢ ሂደት እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው መተግበሪያ ነው፡፡
ይህ አዲሱ መተግበሪያ አሁን በሥራ ላይ ካለው የቴሌብር መተግበሪያ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የአፈጻጸም፣ የሴኩሪቲ ሲስተም፣ ወደ ሲስተም ማስገቢያና ምዝገባ ጊዜ (login & registration time) ፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በማውረድ የስልክ የዳታ የመያዝ አቅም መቀነስ (phone memory consumptions) እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችልና የባዮሜትሪክ ማረጋገጫ (biometric authentication)፣ ማይኢትዮቴል መተግበሪያ እና ሌሎች የአጋሮቻችን መተግበሪያዎችን በማካተት ደንበኞች ወጥ፣ የተቀናጀ፣ ብቁ እንዲሁም የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል እና በአንድ ጊዜ ለደንበኞች ፈርጀብዙ የዲጂታል ግብይት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ነው፡፡
ደንበኞቻችን አዲሱን የቴሌብር ሱፐርአፕ መተግበሪያ ለመጠቀም በቀላሉ ፕሌይ ስቶር ፣ አፕ ስቶር እና አፕ ጋለሪ ላይ በመግባት፣ ነባሩን የቴሌብር መተግበሪያ አሻሽል (update)የሚለውን በመጫን የቴሌብር ሱፐር አፕን በቀላሉ አውርደው መጠቀም ይችላሉ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የቴሌብር ተጠቃሚዎቻችንን እና ሲስተማቸውን ከቴሌብር ጋር በማስተሳሰር የሀገራችንን የዲጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባትና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት እየደገፉ ያሉ ደንበኞቻችን፣ የቢዝነስ አጋሮቻችንን፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ አገልግሎት ሰጭ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን እያመሰገንን ባጠቃላይ በኢኮሲስተሙ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በቀጣይም ሲስተማቸውን እንዲሁም መተግበሪያቸውን ከቴሌብር ሱፐርአፕ ጋር በማስተሳሰር አብረውን እንዲሰሩና
በጋራ የሞባይል ቴክኖሎጂን ጥቅም አሟጠን በመጠቀም ሀብትና የስራ ዕድል እንድንፈጥር በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም