ኩባንያችን የሀገራችንን የዲጂታል ስትራቴጂ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ የቴሌኮም የመሠረተ ልማት ማስፋፊያዎችን እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እና ለህብረተሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የዲጂታል ሶሉሽኖች በስፋትና በቁርጠኝነት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ኩባንያችን የቢዝነስ እና የመንግስት ተቋማት የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ፍላጎቶችን በማሻሻል አሰራራቸው እንዲያዘምኑ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምር እና ወጭ ቆጣቢ አሰራር እንዲተገብሩ በማስቻል ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር የስማርት የመማሪያ ክፍሎችን በተመረጡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቤቶች ማለትም በስምንት አዳሪ ት/ቤቶችና በ33 ልዩ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን አሟልቶ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱን በማዘመን ተማሪዎች ጥራት ያለው እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ፣ ፍትሃዊ የሆነ የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖር እንዲሁም የትምህርት ግብዓቶች እጥረትን ለመቅረፍ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት የትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያቀርቡ፣ የዲጂታል ትምህርት ትራንስፎርሜሽን እንዲተገብሩ፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ፣ መምህር ተኮር የሆነውን የትምህርት አሰጣጥ ወደ ተማሪ ተኮር እና አሳታፊ የሆነ ስርዓት ለማሸጋገር፣ ለትምህርት መሳሪያዎችና ግብዓቶች ግዢ የሚወጡ ወጪዎችን ለማስቀረት እንዲሁም የትምህርት መሳሪያዎችን እጥረት በመቅረፍ ተማሪዎች በቀላሉ በዲጂታል የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻልና በዲጂታል ዕውቀት የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት የላቀ ሚና ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ መምህራን በማንኛውም ሰዓት (Realtime) የተማሪዎችን የትምህርት ሁኔታን በመከታተልና የማስተማር ሂደትን በፍጥነት ለማስተካከል፣ የተማሪዎችን የትምህርት መረጃ በማዕከል (data) ለማግኘት፣ ፈተናዎችን በኦንላይን ለመስጠት፣ የውጤት አሰጣጥ እና ሪፖርቶችን በቀላሉ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሲሆን ለተማሪዎች ደግሞ ከነባራዊው የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ወደ ዲጂታል የመማር ማስተማር ስርዓት በማሻጋገር ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ፣ በአንድ ቦታ ወይም ክፍል የሚሰጠውን ትምህርት በየትኛውም ጊዜና ቦታ በቀላሉ እንዲከታተሉ እንዲሁም በዲጂታል የታገዘና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

ኩባንያችን ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ጋር የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑ እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ የሚያሻሽሉ የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና መሠረተ-ልማቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ማድረጉ ይታወቃል።

ኩባንያችን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና ከክልሉ ልዩ ልዩ የአስተዳደር መ/ቤቶች ጋር በርካታ ስትራቴጂያዊ ስራዎችን በአጋርነት በመከወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም ኩባንያችን የክልሉን የአሰራር ስርዓት ለማዘመን እና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን የቴክኖሎጂ እና መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

 

መጋቢት 23 ቀን 2016 ..         

ኢትዮ ቴሌኮም    

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives