ኢትዮ ቴሌኮም እና የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ  የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር እንዲፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመፈጸም አገልግሎቱን ተግባራዊ አድርገዋል፤ ይህም የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲን የአሰራር ሥርዓት በማዘመን ባለጉዳዮች ያለምንም ውጣውረድ እና እንግልት በኦንላይን አገልግሎት እንዲስተናገዱ እና ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብር ተጠቅመው የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት 15 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ 27 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲሁም ከ7 ሺ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በቀን በአማካይ ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ አዲስ በተተገበረው አሰራር መሠረት ባለጉዳዮች በኤጀንሲው አገልግሎት ካገኙ በኋላ በሚላክላቸው ወይም በሚሰጣቸው የክፍያ ማዘዣ ቁጥር በመጠቀም የመኪና ሽያጭ ውል፣ የስጦታ፣ የውክልና፣ የብድር፣ የማህበር ምስረታ እና ቃለ ጉባኤ የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር (*127#) በመፈጸም አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ ሁሉን አካታች የፋይናንስ አገልግሎት #ቴሌብር መላ – የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት፣ #ቴሌብር እንደኪሴ –የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙት እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅ ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ አይነቶችን የሚጠቀሙበት ሲሆን አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 22.9 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 97 ዋና ወኪሎችን (Master Agents) ፣ 96 ሺህ ወኪሎችና 22 ሺህ ነጋዴዎች /Merchants/ ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ41.03 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ (Transaction Value) ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከ13 ባንኮች ጋር ትስስር (Integration) በማድረግ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ11 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር የተደረገ ሲሆን በሌላ በኩልም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው እፎይታን አጎናጽፏል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives