ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ የሦስት ዓመት LEAD (መሪ) የተሰኘ የሶስት አመት የእድገት ስትራቴጂ በመቅረጽ መተግበር ጀመረ!
ኩባንያችን ላለፉት 4 አመታት የሪፎርም ስራዎችን መስራቱና BRIDGE (ድልድይ) የተሰኘ የሶስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ቀርጾ ሲተገብር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን 2014 በጀት አመት የስትራቴጂ ዘመኑ ማብቂያ እንደመሆኑ በአዲሱ 2015 በጀት አመት LEAD (መሪ) የተሰኘ አዲስ የእድገት ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ተቋማዊ ሪፎርሙ ከተጀመረ በኋላ ከተሰሩ በርካታ ስራዎች መካከል BRIDGE (ድልድይ) ስትራቴጂ ሲሆን ይህም ኩባንያችን በቴሌኮም ውድድር ገበያ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የመሪነት ሚና ለመጫወት እንዲያስችለው ታልሞ የተቀረጸ ሲሆን፤ እንደታለመለትም በርካታ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
በሪፎርሙና በBRIDGE (ድልድይ) አጠቃላይ የስትራቴጂ ዘመን፣ ኩባንያችን በደንበኛ ብዛት የ75.6% እድገት፣ በገቢ የ76% እድገት ያስመዘገበ ሲሆን በውጭ ምንዛሪ ገቢ የ104% እድገት፣ የተጣራ ትርፍ የ142% እድገት፣ በስማርት ቀፎ ብዛት የ125% እድገት አስመዝግቧል፡፡
ኩባንያችን በአጠቃላይ የBRIDGE (ድልድይ) ስትራቴጂ ዘመን፣ የደንበኞችን አቅም ያገናዘበና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ እስከ 86% የታሪፍ ቅናሽ በማድረግ እንዲሁም የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም ወቅታዊነትን የተላበሱ አጠቃላይ 306 ምርትና አገልግሎቶቸ ፤140 አዳዲስ እና 166 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን አሻሽሎ ለደንበኞች አቅርቧል፡፡
ኩባንያችን እነኚህን ውጤቶች የማስመዝገቡና የማስቀጠል ግቡን ለማሳካት የማቋቋሚያ ደንቡን በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲሻሻል አድርጓል፡፡ በዚህም የተቋሙን ካፒታል ወደ 400 ቢሊዮን ብር ያሳደገና በሞባይል ፋይናንስ ዘርፍና ተያያዥ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ለመሳተፍ የሚፈቅድ፣ እንዲሁም በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችለውና ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ የንግድ ድርጅትን ማቋቋም ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ ስራዎች ማከናወን እንዲችል የሚፈቅድ ነው፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኩባንያችን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ በስትራቴጂ ዘመኑ ከ200 በላይ የፕሮጀክት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን የ4G/LTE እና 4G/LTE Advanced ማስፋፊያዎች፣ የሞባይል ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ ሞጁላር ዳታ ሴንተር /Modular Data Center/ ግንባታ፣ እንዲሁም የቢዝነስ ሳፖርት ሲስተም (Next Generation Business Support System፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት፣ የ5G ኔትወርክ አገልግሎት በዋናነት የሚጠቀሱና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ሀገራዊ ተግባራት ላይ ካለው ተሳታፊነት ባሻገር ለመንግስት በተለያየ መልክ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ ተቋም እንደመሆኑ አጠቃላይ ባለፉት አራት አመታት 86.6 ቢሊዮን ብር ታክስና 11.5 ቢሊዮን ብር ዲቪደንድ ገቢ በማድረግ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ለመወጣት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች ብድር 34.3 ቢሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸም ከአጋሮቹ ጋር ያለውን መልካም የቢዝነስ ግንኙነት፣ ተዓማኒነት እና አጋርነት ማስቀጠል ችሏል፡፡
በስትራቴጂ ዘመኑ ኩባንያችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፋይናንስ ሪፖርቱን በዓለማቀፍ የሪፖርት አቀራረብ ስርአት (IFRS) ማውጣት የቻለ ሲሆን አጠቃላይ እ.ኤ.አ ከ2018 እስከ 2020 ያለው የሂሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተሮች ተመርምሮ ከትችት የፀዳ ወይም እንከንየለሽ (Unqualified) በሚል የኦዲተር አስተያየት ሊያልፍ ችሏል፡፡
ኩባንያችን ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰባችን ፋይዳ ባላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልኩ በሚገባ የተወጣ ሲሆን በሶስቱ ዓመታት በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 2.72 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገራችን በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ከመሳተፉ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከ 44.7 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡
በአጠቃላይ ሪፎርሙና ስትራቴጂው የታለመላቸውን ዓላማ በማሳካት ተቋማዊ አቅም በመገንባት፣ የአሰራር ሥርዓትን በማጠናከር፣ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት የአስቻይነት ሚና በመጫወት በተቋማትና በግለሰቦች ህይወት ላይ መልካም አሻራ ያሳረፉ እና በስኬት የተጠናቀቁ ነበር፡፡
LEAD (መሪ) የእድገት ስትራቴጂ
ኩባንያችን በአዲስ ጅማሮ በአዲስ እይታ ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር (beyond connectivity) የዲጂታል እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የድርጅቶችን እንዲሁም የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት
እንቅስቃሴ በማሳለጥ አካታች እድገት እንዲኖር የማስቻል ራዕይ የሰነቀ LEAD (መሪ) የተሰኘ የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ቀርጾ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 01 ቀን 2022 ጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ የመሪነት ሚና በመጫወት የሀገራችን የቴሌኮም ዘርፍ የማህበረሰባችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲኖረው የማስቻል ታላቅ ዓላማን ያነገበ ነው፡፡
ስትራቴጂው ሲዘጋጅ የኩባንያችንን ተወዳዳሪነት እና አስተማማኝ እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተቋሙ ላይ ፍላጎትና ተጽዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ የመንግስት የፖሊሲ ሰነዶችን፣ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ፍላጎትና ተጽዕኖ (የደንበኞች፣ የሠራተኞች፣ የተቆጣጣሪ አካላት፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የተለያዩ የመንግስት አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት) በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች ተቋማት ያላቸውን የገበያ እንቅስቃሴና ልምድ፣ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ እድገት ዋና ዋና አዝማሚያዎችና የዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመተንተን፣ የተወዳዳሪ ኩባንያዎችን ስትራቴጂዎች እንዲሁም የኩባንያችን ውስጣዊ ጥንካሬና ውስንነቶችን በመለየት፣ ውጫዊ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶችን በመለየትና በመተንተን የተቋሙን ተጨባጭ አቅምና ለተወዳዳሪነት የሚያበቃውን ተግባራት በመቃኘት የተዘጋጀ እቅድ ነው፡፡ እነዚህ ዘርፈ ብዙ ምልከታዎችና ከባቢያዊ ሁኔታዎች ትንተና ከተከናወነ በኋላ በአጠቃላይ ወደ 20 ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች በመለየት በመጨረሻም ስድስት ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች ተቀርጸዋል፡፡
ይህ ስትራቴጂ የቴሌኮም ዘርፍ በፍጥነት እያደገና ተለዋዋጭ በመሆኑ ከወቅቱ ጋር በፍጥነት የሚራመድ ተቋም የመሆን ትልም በመንደፍ ይህ ዕቅድ ቋሚ (Static) ሳይሆን በየወቅቱ በኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩ እድገትና ለውጦች እንዲሁም ከውድድር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ‘deliberate’ እና ‘emergent strategy approach’ በመከተል የተዘጋጀ ሲሆን ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች ሲለወጡ በድጋሚ ታይቶ እቅዱ በለውጡ መሰረት የሚሻሻል ይሆናል፡፡
በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ ላለፉት 128 ዓመታት ኩባንያው ይዞት የነበረውን ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴት አሁን ከደረሰበት ወቅታዊ ተቋማዊ አቅም፣ የገበያና የኢንዱስትሪ ሁኔታ እንዲሁም በውድድር ገበያ አሸናፊና ቀዳሚ የመሪነት ሥፍራ እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ የተቀየሩ ሲሆን እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
ራዕይ/Vision
መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ
A Leading Solutions Provider
ተልዕኮ/ Mission
አስተማማኝ የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በማቅረብ ሕይወትን ማቅለል እና የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን
Provide Reliable Communications & Digital Financial Services to Simplify Life, and Accelerate Digital Transformation of Ethiopia.
እሴት/ Values
- ሰው ተኮር/ Human- Centric
- ታማኝነት/ Integrity
- ልህቀት/ Excellence
- ማህበራዊ ኃላፊነት/ Socially Responsible
- አብሮነት/ Togetherness
የውድድር ገበያውን በብቃት ለመወጣት በተለዩት ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች ማለትም ምርጥ የደንበኛ ተሞክሮን ማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ እድገት፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማረጋገጥ፣ ሰው ተኮርና ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ተቋም መገንባት፣ የኦፕሬሽን ልህቀት እና ቀዳሚ ተቋማዊ ገጽታ ግንባታ ሥራዎች ኩባንያው ዕውን ለማድረግ ያለውን የሰው ኃይል፣ እውቀትና ሀብት በአግባቡ በመምራት በደንበኞቹ፣ በአጋሮቹና በባለድርሻ አካላት ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡
ስትራቴጂው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የደንበኛ ፍላጎትን ለማርካት፣ የቴሌኮም ስርጸትን በማሳደግ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመደገፍና አጠቃላይ የሀገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የተቋሙን የገቢ ምንጭ ከተለመደው መሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ወደ ዳታና የይዘት አገልግሎቶች ትኩረት በማድረግ፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር እና አዳዲስ የስራ መስኮችን በማስጀመር በሁሉም ዘርፍ ዝግጅት በማድረግና ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በማጠናከር የተቋሙን ቀጣይነትና እድገት አስተማማኝ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በወድድር ገበያው የኩባንያችን ህልውና የሆኑትን ደንበኞቹን በአገልግሎቶቻችን በማርካትና ከኩባንያችን ጋር ረዥም ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የአገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የመረጡትን የአገልግሎት አይነት መጠቀም እንዲችሉ የአገልግሎትን በማስጀመር ተደራሽነትን የማሳደግ፣ የድህረ-ሽያጭ አገልግሎቶችን በማሻሻል ደንበኞቻችን የተሻለ ተሞክሮ እንዲኖራቸው የማስቻል እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትን የኔትዎርክ ዴንሲቲ የሚያሳድጉ የኔትዎርክ ማስፋፊያ ፕሮግራሞችን በመተግበር የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማርካት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን አጋርነት አጠናክሮ በመቀጠል፣ የስማርት ፎንና ሌሎች ደንበኞች የደንበኛ መገልገያ መሳሪያዎች በተራዘመ ጊዜ የክፍያ አማራጮች (installment plan) በመጠቀም ልዩ ልዩ አማራጮችን ለገበያ በማቅረብ የደንበኛን ተሞክሮ የማሻሻል ስራዎች ለማከናወን ታቅዷል፡፡
ብቁ፣ ምርታማና ስነምግባር የተላበሰ የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር የኢንዱስትሪውን በፈጣን ሁኔታ ማደግና ተለዋዋጭነትን በሚገባ የሚገነዘብ፣ ከእድገቱ የሚገኙ ትሩፋቶችንና መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ የሚጠቀም እንዲሁም ከኢንዱስትሪው ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና መጭውን የውድድር ገበያ በበቂ ዝግጅትና በጥንቃቄ ለመምራት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል መገንባት የስትራቴጂው ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡
በቴሌኮም ቢዝነስ ዘርፍ ዙሪያ ከሚሰራ የኢንዱስትሪው ተዋናይ ባለድርሻ አካላት ጋር በተለይም የቴክኖሎጂ መሳሪያ አቅራቢዎች፣ ከኩባንያችን ምርት አከፋፋይ አጋሮች፣ የይዘት አገልግሎት አቅራቢዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በስትራቴጂው ዙሪያ ውይይት በማድረግ ተጨማሪ ግብዓቶች የሚገኝበት እንዲሁም ምርትና አገልግሎቶቻችንን ወደ ገበያ የምናቀርብበትን ጊዜ የሚያሳጥርና የደንበኞቻችንን እርካታ ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት የሚደግፍ ከመሆኑም ባሻገር በውድድር ገበያው በባለድርሻ አካላትና በአጋሮቻችንም ጭምር ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን የሚያስችል እና ተጨማሪ ግብዓቶችን በማግኘት የተሻለ አጋርነት የሚፈጠርበት ይሆናል፡፡
በስትራቴጂ ዘመኑ እንደ ስጋትና ተግዳሮት የተወሰዱ ዋና ዋና ጉዳዮች ፡ ከጸጥታ ጋር በተገናኘ አገልግሎት መስጠት አለመቻል፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ የገበያ ውድድር፣ የገበያ አለመረጋጋትና የዋጋ ግሽበት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የአቅርቦት ተግዳሮቶች፣ የመሠረተ ልማት ውድመት፣ የቴሌኮም ማጭበርበርና የሳይበር ጥቃቶች፣ የሬጉላቶሪ ጉዳዮችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በስትራቴጂው የተለዩ ስጋቶችና ተግዳሮቶች ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ አቅጣጫና መርሃ ግብር እንዲሁም ፈጻሚ የሥራ ክፍል ተመድቦ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ በእቅድ የተያዘ ሲሆን ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል፡፡
ኩባንያችን በ2015 በጀት ዓመት የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉና ተሞክሮን የሚያሻሽሉ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ ሁለገብ ጥረቶች ለማከናወን የታቀደ ሲሆን በተለይም የኩባንያውን የገበያ ድርሻ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የኔትወርክና የሲስተም አቅም ማሳደጊያና ማሻሻያ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የሚተገበሩ ይሆናል፡፡ በዚህም የዳታ ትራፊክ እድገትን መሠረት ያደረገ የ3ጂ እና የ4G/LTE Advanced አገልግሎት ኔትዎርክ አቅምና ሽፋን ማሳደጊያ ሥራዎች፣ የ5ጂ ቅድመ ገበያ ማስፋፊያ፣ የባክሃውልና ትራንስፖርት ኔትወርክ አቅም ማሳደጊያ ሥራዎች፣ የመደበኛ ብሮድባንድ አቅም ማሳደጊያ፣ የኢንተርፕራይዝ፣ ሶሉሽንስ፣ የሞባይል መኒ እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ የክላውድ አገልግሎት፣ የኦፕሬሽንስ ሰፖርት እና የኮርፖሬት
ሶልዩሽንስ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የሴኩሪቲ ሶልዩሽንስ እና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እና የተለያዩ የሲቪል ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር እቅድ ተይዟል፡፡
በዚህ በጀት ዓመት በአጠቃላይ 8 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የሞባይል ኔትወርክ አቅም በመገንባት የደንበኛ ብዛትን በ10.3% በመጨመር 73.5 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን በሞባይል 10.5% በመጨመር 71 ሚሊዮን እንዲሁም የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኛ በ37.4% በመጨመር 696.7 ሺህ በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 68% ለማድረስ ታቅዷል፡፡
ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከተለመደው የቴሌኮም የገቢ ምንጮች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶችን በመጨመር፣ አዳዲስ እና የተሻሻሉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ፣ የቴሌብር ተደራሽነትና የአገልግሎት አይነቶች እንዲሁም አጋሮችን በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል እና የደንበኛ እርካታን፣ ቆይታንና ታማኝነትን በማሳደግ የ2015 በጀት ዓመት አጠቃላይ የገቢ መጠንን በ22.4% በማሳደግ 75.05 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዷል፡፡
ኩባንያችን የ2015 በጀት አመትን አዲስ ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ሁለት ወር ያስቆጠረ ሲሆን በመጀመሪያው ሁለት ወራት የዕቅዱን 98% አሳክቷል፡፡ የኩባንያችን ህልውና የሆኑትን ደንበኞቹን ለማርካትና ለማቆየት የሚያስችሉ በአባሪ የተያያዙትን በርካታ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ይዞ ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም ኩባንያችን ባለፈው የስትራቴጂ ዘመን ላስመዘገበው አበረታች ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ ምርትና አገልግሎቶቻችንን አከፈፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ እያልን ሁልጊዜም ለደንበኞቹ እርካታ የሚተጋው ኩባንያችን ቀጣዮቹንም አመታት በላቀ አገልግሎት ከእናንተ ከደንበኞቹ ጋር አብሮ ለመዝለቅ ተዘጋጅቷል፡፡
መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም
አብሮነት በላቀ አገልግሎት!
መልካም አዲስ አመት! መልካም የስራ ዘመን ይሁንልን!
ኢትዮ ቴሌኮም