ኩባንያችን በትምህርቱ ዘርፍ ያለውን የዲጂታል ክፍተት በማጥበብ የማህበራዊ ሃላፊነቱን አሻራ ማሳረፋን አጠናክሮ በመቀጠል፣ የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎችን በዕውቀት ለማነጽ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በዛሬው ዕለትም የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ተግባራዊ ያደረገውን ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች የእንግሊዚኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲማሩ የሚያስችል የተማሪዎች አጋዥ የድረ-ገጽ ትምህርት አገልግሎት ከክፍያ ነጻ እንዲሰጥ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህም በእነዚህ የክፍል ደረጃዎች የሚማሩ ተማሪዎች የትምህርት አጋዥ ቪዲዮዎችን በነጻ እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፤ ለዚህም በወር እስከ 3.75 ቢሊዮን ብር የሚገመት ወጪን የሚሸፍን ይሆናል፡፡

በዚህ ፕሮግራም ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያሉ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን፤ ተማሪዎች https://learn-english.moe.gov.et/ በመጠቀም የእንግሊዚኛ ቋንቋ የቪዲዮ ትምህርቶችን በነጻ በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ መከታተል እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶቻቸውን፣ ብቃታቸውን እና ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ በኩል የላቀ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ኩባንያችን ከምንጊዜውም በላይ ለትምህርት ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ ለአብነትም በቅርቡ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ጦርነት ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለማቋቋም እና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ በአጭር የጽሁፍ መልእክት (9222) እና በቴሌብር መተግበሪያ አማካኝነት ድጋፍ ሰጪዎች አቅማቸው የፈቀደውን የገንዘብ መጠን ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ዘዴ ማመቻቸቱ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም በመላ አገሪቱ ለሚገኙ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ45.48 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን፣ ጠረጴዛዎችና ወንበሮችን፣ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን በማሟላት የዲጂታል የመማሪያ ማዕከሎቹን ያቋቋሙ ሲሆን በዚህም ከ140,596 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ አድርጓል፡፡  

የትምህርቱ ዘርፍ ለሀገራችን ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴ ያለውን ፈርጀ-ብዙ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት ኩባንያው ከዚህ ቀደም የትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈና ጥራት ያለው ትምህርት በቀጥታ ስርጭት እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ከፍተኛ አቅም ባላቸው የገመድ እና የሳተላይት መገናኛ አማራጮችን በማገናኘት (ስኩል ኔት)፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በነጻ እንዲሁም እስከ 86 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ በማድረግ ከ4.8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያችን በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ360 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 60,567 ተማሪዎች በ54.3 ሚሊየን ብር በመግዛት 726.8ሺ የመማሪያ ደብተሮችን ድጋፍ አድርጓል፡፡ እንዲሁም በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ665 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች 16.5 ሚሊየን ብር የሚገመት 50,000 ደርዘን የመማሪያ ደብተሮችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የለገሰ ሲሆን በ24 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 9,000 ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር 23.4 ሚሊየን ብር፣ በ45 ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረጡ 5,500 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የኪስ ገንዘብ 22 ሚሊዮን ብር መድቦ ለእያንዳንዱ ተማሪ በወር 400 ብር ድጋፍ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር ሴቶች የመረጃ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመደገፍ 54.4 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ 70 ሺህ የሞባይል ቀፎዎችን ከሲም ካርድ ጋር በአገራችን 846 ወረዳዎች ለሚገኙ ሴቶች በስጦታ ማበርከቱ እንዲሁም ሴት መምህራንን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደግፈው በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመደገፍ 50 ላፕቶና 200 ዘመናዊ የስልክ ቀፎ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሴት መምህራን ሽልማት መስጠቱ ለትምህርቱ ዘርፍ ልህቀት ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው፡፡

ኩባንያችን እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ እና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም በማህበረሰቡ ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ሀገራዊ አለኝታነቱንና ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ህዳር 2 ቀን 2015

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives