ኩባንያችን የሀገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍና የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት አገልግሎቱን ዘመን አፈራሽ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች የመደገፍና ቀጣይነት ባለው መልኩ የቴክኖሎጂ እድገትን በመከተል እንዲሁም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር (Beyond Connectivity) የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችንና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን፣ በራዕዩና በተልዕኮው እንዲሁም በሦስት ዓመት ሊድ (LEAD) ስትራቴጂው ላይ እንደተመለከተው መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ በመሆን የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን ከሚተገብራቸው በርካታ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሆነውን ክላውድ ላይ የተመሠረተ የኮንታክት ሴንተር አገልግሎቱን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡

የኮንታክት ሴንተር አገልግሎት ከዚህ ቀደም ደንበኞችን በድምፅና በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተናጠል ያስተናግዱ የነበሩ የጥሪ ማዕከሎችን አሰራር ያዘመነና በልዩ ልዩ አማራጮች ማለትም በድምጽ፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ በኢሜይል፣ በድህረ ገጽ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም ቻትቦትን (chatbot) በመጠቀም የሚቀርቡ የደንበኞችን ጥያቄያዎች በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለኮንታክት ሴንተር ወኪሉ ማቅረብ በማስቻሉ የቢዝነስ ተቋማት ቀልጣፋና ተደራሽ የደንበኞች አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡

የኮንታክት ሴንተር አገልግሎት ድርጅቶች ደንበኞቻቸው የሚስተናገዱባቸውን ልዩ ልዩ አማራጮች ይዞ በመቅረቡ ወደ ጥሪ ማዕከል ደውለው ወረፋ በመጠበቅ የሚጠፋ ጊዜን በመከላከልና ደንበኞች በማንኛውም ጊዜና ሰዓት በፈለጉት አማራጮች መስተናገድ የሚያስችል እንዲሁም የደንበኞቻቸውን ተሞክሮ እና እርካታ የሚያሳድግ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቶች ደንበኞቻቸው የትኛውንም አይነት አማራጭ ተጠቅመው የተስተናገዱ ቢሆን፤ የኮንታክት ሴንተር ወኪሉ በየቻናሉ የጠየቁትን ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ላይ ማየት ስለሚችል የደንበኞቻቸውን ፍላጎት በብቃት እንዲያስተናግዱ በማድረግ የደንበኞችን እርካታ መጨመር ያስችላል፡፡

ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በጥሪ ማዕከሎቻቸው በድምፅ ብቻ ይቀበሏቸው የነበሩትን የደንበኞች አስተያየት መስጫ አማራጮችን በማስፋት ልዩ ልዩ እይታዎችን በሚሰጡ እንደ customer satisfaction score, net promoter score and customer effort score ያሉ መመዘኛዎችን ተጠቅመው የአገልግሎታቸውን ጥራት መለካት በማስቻሉ ድርጅቶች መረጃ ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን እንዲያከናውኑ ያግዛል፡፡

በተጨማሪም ይህ አገልግሎት ድርጅቶች የራሳቸውን የጥሪ ማዕከል መገንባት ሳያስፈልጋቸው እንዲሁም ተጨማሪ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ መቅጠር ሳያስፈልጋቸው ዘመናዊና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፍላጎትን ተከትሎ መስፋፋት የሚችል እና ወጪ ቆጣቢ  የኮንታክት ሴንተር እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኮንታክት ሴንተር አገልግሎታችንን በመጠቀም የደንበኞቻቸውን ተሞክሮ ለማሻሻል የሚሹ የድርጅት ደንበኞች ወደ ኢንተርፕራይዝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከሎቻችን ቀርበው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ በአክብሮት እየገለጽን፣ በቀጣይም ዓለማችን የደረሰበትን ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድ ደንበኞቻችን ተደራሽ በማድረግ ሕይወትን የማቅለል፣ ቢዝነስን የማሳለጥ እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ተግባራችንን የምንቀጥል መሆኑን እንገልጻለን፡፡

                                            ጥቅምት 08 ቀን 2015 ዓ.ም

                                                       ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives