ኢትዮ ቴሌኮም የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የዓለማችን የቴክኖሎጂ የመጨረሻ ደረጃ የሆነውን የአምስተኛውን ትውልድ የሞባይል አገልግሎት በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በጂግጂጋና በድሬዳዋ ከተሞች ለአገልግሎት ያበቃውን ይህንኑ የ5ኛ ትውልድ የሞባይል አገልግሎት በኢትዮ ቴሌኮም ማዕከላዊ ምሥራቅ ሪጂን በሐረር እና በሀሮማያ ከተሞች በመዘርጋት በይፋ ማስጀመሩን በታላቅ ደስታ ይገልጻል፡፡
በዚህም መሠረት የ5ኛ ትውልድ የሞባይል አገልግሎቱን በአምስት የማዕከላዊ ምሥራቅ ሪጂን አካባቢዎች ያስጀመረ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል በሐረር ከተማ በሚገኙ አራት አካባቢዎች ማለትም በራስ መኮንን ትምህርት ቤት፣ በአራተኛ፣ በጀጎል እና ራስ ሆቴል/አጂፕ አካባቢ እንዲሁም በሀሮማያ ከተማ አገልግሎቱን አስጀምሯል፡፡
በዚህም መሠረት የ5ኛ ትውልድ የሞባይል አገልግሎቱን በአምስት የማዕከላዊ ምሥራቅ ሪጂን አካባቢዎች ያስጀመረ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል በሐረር በሚገኙ አራት አካባቢዎች ማለትም በራስ መኮንን ትምህርት ቤት፣ በአራተኛ፣ በጀጎል እና ራስ ሆቴል/አጂፕ አካባቢ እንዲሁም አንዱን በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አገልግሎቱን አስጀምሯል፡፡የ5ጂ አገልግሎት ሥራ ላይ መዋል የቢዝነስ ደንበኞቻችን ምርታማነታቸውን እና የአሠራር ቅልጥፍናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ፣ በዘመናዊ መተግበሪያዎች አማካኝነት አዳዲስ ገቢዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል፣ የቢዝነስ ትንታኔን በቀላሉ በማግኘት ከንግድ ለውጦች ጋር በፍጥነት እንዲላመዱ እገዛ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ተለዋዋጭ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ለተልዕኮ-ወሳኝ የሆነ ፈጣን የዳታ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፣ የማሕበረሰባችንን ሕይወት በማቅለል በኩልም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት ለዘመናዊ ቤት (Smart home)፣ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና የሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ትምህርት፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ እንዲሁም በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የ5ጂ ጌሞች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የዘመናችን የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ (Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ (Ultra-low latency) ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
በተለይም ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት (real time) መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና እና ህክምና ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ እንደ ሹፌር-አልባ ተሽከርካሪዎች (self-driving vehicles) ፣ Internet of Things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችም በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አስተማማኝ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ኩባንያችን ለክቡራን ደንበኞቹ የ5ጂ ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ የመኖሪያ ቤት ዳታ እንዲሁም የተለያዩ የ5ጂ ጥቅል አማራጮችን ያቀረበ ሲሆን፣ ደንበኞች የ5ጂ አገልግሎትን መጠቀም በሚያስችሉ መሳሪያዎችና ቀፎዎች አማካይነት አገልግሎቱን የሚችሉ መሆኑን በታላቅ ደስታ እንገልጻለን፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም