የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይን ዕውን ለማድረግ እና በ128 ዓመታት በአብሮነት ጉዟችን ስናደርገው እንደነበረው ሁሉ ህዝባችንን የወቅቱን ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ለማድረግ የመጨረሻውን የ5ኛ ትውልድ ኔትወርክ (5G) ዛሬ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በሙከራ ደረጃ አገልግሎቱን ማሰጀመራችንን በደስታ እንገልጻለን፡፡

ኩባንያችን ባለፉት ወራት የ5ኛ ትውልድ ኔትዎርክ (5G) አገልግሎት በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንኑ አገልግሎት በአዳማ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች በሙከራ ደረጃ በማስጀመር የስነ-ምህዳሩን (ecosystem) ዝግጁነት የመፈተሽ ሥራ በማከናወን አገልግሎቱን ገበያ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን (real time) ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው እና Internet of Things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አስተማማኝና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የአዳማ ከተማን ስማርት ሲቲ ከማድረግ አኳያ የተያዘውን እቅድ በማሳካት የከተማዋን ሁለንተናዊ አንቅስቃሴ በስማርት ቴክኖሎጂ በማሳለጥ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

በተለይም የ5ጂ የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት ደንበኞቻችን ምርጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የላቀ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ የኢንተርፕራይዝ ደንበኞቻችን ደግሞ የአሰራር ቅልጥፍናቸውንና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ሚና የሚጫወትላቸው ይሆናል፡፡

የ5ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ቀደም ሲል ከነበረው ቴክኖሎጂ ትውልድ (የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ) እጅግ የላቀ አቅም ያለው እና ፈርጀ-ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህም እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት የሚመጥን ብቻ ሳይሆን የሃገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ እና ቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እንዲሁም የማህበረሰባችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ይሆናል፡፡

ኩባንያችን በቀጣይም አገልግሎቱን በስፋት ገበያ ላይ ለማዋልና የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን የደንበኞችን ዝግጁነትና 5ጂ የመጠቀም ፍላጎት ማደግ፣ 5ጂ መጠቀሚያ መሳሪያዎችና የ5ጂ መጠቀሚያ ቀፎዎች በስፋትና አቅምን ባገናዘበ መልኩ ገበያ ላይ መኖር፣ በሀገራችን ያሉ ኢንዱስትሪዎች 5ጂ አገልግሎትን የመጠቀም ፍላጎትና ዝግጁነት እንዲሁም አጠቃላይ የቴሌኮም ስነ-ምህዳር የእድገት አዝማሚያን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሌሎች የክልል ከተሞች ተጨማሪ ማስፋፊያዎችን በማከናወን አገልግሎቱን የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

                               

                                  ኢትዮ ቴሌኮም

                         ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም

 

 

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives