ኢትዮ ቴሌኮም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለጉዳዮች የሰነድ ማረጋገጫ አገልግሎት ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ደንበኞች ደግሞ የምዝገባ፣ የምዝገባ እድሳት እና የጊዜያዊ ምስክር ወረቀት የአገልግሎቶችን ያለምንም ውጣውረድ በኦንላይን ባለጉዳዮቻቸው አገልግሎት እንዲያገኙ እና ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው የአገልግሎት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት ባለጉዳዮች በቅድሚያ www.eservices.gov.et ላይ በመግባት እና የሚፈልጉትን የአገልግሎት ሰጪ ተቋምና የአገልግሎት አይነት በመምረጥ እንዲሁም የአገልግሎት ቅጹን በቀጥታ (online) ከሞሉ በኃላ ለአገልግሎት የክፍያ አማራጭ ቴሌብርን በመምረጥ እና ቀጣይ ሂደቶችን በመከተል ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ #ቴሌብር መላ – የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት፣ #ቴሌብር እንደኪሴ የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙት እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅ ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ ዓይነቶችን የሚጠቀሙበት ሲሆን አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት ፋይናንስ ለሁሉም በሚል መርህ በማቅረብ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 23.4 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 97 ዋና ወኪሎችን (Master Agents) ፣ 81 ሺህ ወኪሎች 22 ሺህ ነጋዴዎች /Merchants/ ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ50.97 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ (Transaction Value) ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከ14 ባንኮች ጋር ትስስር (Integration) በማድረግ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ11 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው እፎይታን አጎናጽፏል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡     

                                              ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም

                                                     ኢትዮ ቴሌኮም

 

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives