ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ መጠነ-ሰፊ ስራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን እየገፋበት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለጉዳዮች ከንግድ ምዝገባ፣ ከንግድ ፈቃድ እና ከንግድ ስያሜ ጋር ተያያዥነት ላላቸው የአገልግሎት ክፍያዎች ያለምንም ውጣውረድ በኦንላይን አገልግሎት እንዲያገኙ እና ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው የአገልግሎት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡

በተለይም የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለጉዳዮች ለአዲስ ንግድ ምዝገባ፣ ማሻሻያ፣ ምትክ እና የውል ማቋረጥ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲሁም አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ ምትክ ለመውስድ፣ ውል ለማቋረጥ/ለመሰረዝ፣ ለአዲስ የንግድ ስም፣ የንግድ ስም ለማሻሻል፣ ለመቀየር እና ለመሰረዝ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር የክፍያ አማራጭ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል፡፡

ባለጉዳዮች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ www.etrade.gov.et በመግባት እና የሚፈልጉትን የአገልግሎት አይነት በምረጥ እንዲሁም የአገልግሎት ቅጹን በቀጥታ (online) በመሙላት ለአገልግሎቱ ክፍያ ለመፈጸም የሚሰጣቸውን የመክፈያ ቁጥር በመጠቀም በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በቴሌብር አጭር ቁጥር (*127#) የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ መፈጸም ይችላሉ፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ #ቴሌብር መላ – የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት፣ #ቴሌብር እንደኪሴ የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙት እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅ ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ ዓይነቶችን የሚጠቀሙበት ሲሆን አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት ፋይናንስ ለሁሉም በሚል መርህ በማቅረብ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 24.9 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 101 ዋና ወኪሎችን (Master Agents) ፣ 87 ሺህ ወኪሎች 23 ሺህ ነጋዴዎች /Merchants/ ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ101.1 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ (Transaction Value) ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከ16 ባንኮች ጋር ትስስር (Integration) በማድረግ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ13 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው እፎይታን አጎናጽፏል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives