ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል (Modular Data Center) ገንብቶ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ መጠቀም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ይህንኑ ከፍተኛ አቅም ያለውን የመረጃ ማዕከል በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ከዘመን ባንክ፣ ዘምዘም ባንክ፣ ሂጅራ ባንክ፣ ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ እና ዌብስፕሪክስ ጋር ተፈራርሟል፡፡

ይህም የተቋማቱን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በዚህ እጅግ ዘመናዊ እና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ የመረጃ ማዕከል አማካኝነት አስተማማኝ እና ወጥ የሆነ አገልግሎት ለደንበኞቻቸው ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡

ዘመናዊ የመረጃ ማዕከሉ የራሱ ከፍተኛ መጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ያለው፣ እጅግ ጠቀሜታ ያለውን የዳታ አገልግሎት ማስቀመጥ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራ ከፍተኛ አቅም ያለው የዳታ ማዕከል ሲሆን፣ አገልግሎት እንዳይስተጓጎል የሚያስችል 99.99 በመቶ አስተማማኝ የኔትዎርክ አቅም ያለው እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሲስተሞች ላይ የኔትዎርክ ኮኔክሽንም ይሁን ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ቢያጋጥሙ ፈጣን ፍተሻና ጥገና ለማከናወን የሚያስችል ሥርዓት ያለው እጅግ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ነው፡፡

በተጨማሪም ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ ኃይልን የሚቆጥብ የኤሌክትሪክ ሲስተም፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቆጣቢ፣ የማቀዝቀዣ ሲስተምና የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙለት ሲሆን ዘመናዊ የሆነ የኔትዎርክና የፋይበር ኬብል ማቀፊያዎች እና ኮምፓርትመንቶች ያሉት ነው፡፡ እንዲሁም ማዕከሉ እጅግ ጠንካራ በሆነ የፋይበር ኮኔክሽን የተገነባ በመሆኑ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶችን መስጠት ለሚፈልጉ ድርጅቶች በአጭር ጊዜ የመረጃ ቋቱን በመጋራት ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል፡፡

የዳታ ማዕከሉ አዳዲስ ፕላትፎርምና አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችል ተለዋዋጭ የቴክኖሎጂ ባህሪ ያለው፣ ደንበኞች ለሚያካሄዱት ቢዝነስ አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም ለክላውድ አገልግሎት ፈላጊዎች ወይም አጋሮች በኮሎኬሽን አማካይነት በፈጣን ሁኔታ ለመገብየት እና ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ እና ለላቀ የደንበኛ አገልግሎት ተሞክሮ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ተቋማቱ ለሚያከናውኗቸው ዘርፈ-ብዙ አሰራሮች እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ በተለይም ኩባንያችን አገልግሎት ለሚሰጥባቸው ለሁሉም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅና የኔትዎርክ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ በተጨማም ለኩባንያዎች፣ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ቢዝነሶች እንዲሁም ለአዳዲስ ቢዝነስ ጀማሪዎች በስራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ የስራ ብቃታቸው፣ ተወዳዳሪነታቸው እና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በአስተማማኙ የመረጃ ማዕከላችንን ለመጠቀም ፈቃደኛ ስለሆናችሁ ዘመን ባንክ፣ ዘምዘም ባንክ፣ ሂጅራ ባንክ፣ ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ እና ዌብስፕሪክስ የቦርድ አመራሮች እና ሥራ አስፈጻሚዎችን ከልብ እያመሰገንን በተመሳሳይ መልኩ ይህንን የሞጁላር መረጃ ማዕከል (Modular Data Center) መጠቀም የምትፈልጉ የድርጅት ደንበኞቻችን ወደ ኢንተርፕራይዝ የሽያጭ ማዕከሎቻችን ቀርባችሁ አገልግሎቱን ማግኘት እንደምትችሉ በደስታ እንገልጻለን፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም

 

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives