ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ለህብረተሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ ትርጉም ያላቸውን የዲጂታል ሶሉሽኖች ለማቅረብ ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም ግለሰቦችና ድርጅቶች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲሁም ቢዝነሶቻቸውን የበለጠ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉና ሀገራዊ ፋይዳ የሚያመጡ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ የደንበኞቹን የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ፍላጎቶችን በማሟላት የላቀ ተሞክሮ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘመን አፈራሽ አገልግሎቶችን በየጊዜው በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም መሠረት ኩባንያችን በዛሬው ዕለት የደንበኞችን ተሞክሮ በእጅጉ የላቀ የሚያደርጉ አራት አገልግሎቶችን በይፋ አስጀምሯል፡፡
1. የቮልቲኢ አገልግሎት (VoLTE)፡- ኩባንያችን በበርካታ የሃገራችን ከተሞች የ4ጂ ኔትወርክ አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን እና የስማርት ስልኮች ስርጭት መጨመርን ተከትሎ በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ስታንዳርድ መለኪያ የሆነውን እና ደንበኞች ከተለመደው የድምጽ ጥሪ አገልግሎት እጅግ የላቀ የድምጽ እና የምስል ጥራት (HD calls) ያለው የስልክ ጥሪ ለማድረግ ወይም ለመቀበል የሚያስችላቸው ቮልቲኢ (VoLTE- Voice over Long-Term Evolution) የተሰኘ ዘመናዊ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡
ቮልቲኢ አገልግሎት በፍጥነት የስልክ ጥሪ ለማከናወን (Instant Call Setup)፣ ያለምንም የአካባቢ የድምጽ ብክለት (noise) ጥራት ያለው የድምጽ ጥሪ ለማድረግ፣ ዳታ/ኢንተርኔት ሳያበሩ የድምጽ ወይም የምስል (video) ጥሪዎችን በመቀያየር በተሻለ የባትሪ የቆይታ ጊዜ አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችል ነው፡፡
በተጨማሪም ደንበኞች ዳታ/ኢንተርኔት እየተጠቀሙ ስልክ በሚደወልላቸው ጊዜ ያለምንም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ወይም ፍጥነት መቀነስ ጥሪዎችን መቀበል የሚችሉ ሲሆን፣ ቮልቲኢ የቪዲዮ ጥሪ አገልግሎት ከነባሩ የድምጽ የአገልግሎት ታሪፍ ጋር ተመሳሳይ ከመሆኑ ባሻገር አገልግሎቱን ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ማስጀመር ይችላሉ። በተጨማሪም ደንበኞች በውጭ ሀገር በሚጓዙበት ጊዜ አስተማማኝ የሮሚንግ ለማግኘት እንዲሁም የኢንተርኮኔክት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ቮልቲኢ (VoLTE) ለመጠቀም የሚያስችሉ የስማርት ስልክ እና የ4ጂ/5ጂ ሲም ካርድ የሚያስፈልግ ይሆናል።
- ሪች የኮሙኒኬሽን አገልግሎት/ ሪች ቢዝነስ መልዕክት አገልግሎት/ Rich Communication Service/ Rich Business Messaging (RCS/RBM) አገልግሎት የግለሰብ እና የቢዝነስ ደንበኞች የመደበኛ የመልዕክት አገልግሎትን ተጠቅመው ከጽሁፍ መልዕክት ባሻገር የፎቶ ወይም የቪዲዮ መረጃዎችን፣ ኢሞጂዎችን፣ የድምጽ ክሊፖችን፣ የአድራሻ (location Information) እና በርካታ አሁናዊ (realtime) መረጃዎችን የሞባይል ዳታን ወይም ዋይፋይን በመጠቀም ለማጋራት የሚያስችል የአገልግሎት አይነት ነው፡፡ አገልግሎቱ ያልተገደበ የጽሑፍ መልዕክት ለመላክ፣ የቡድን ውይይት /group chat/ እና የቪዲዮ ጥሪዎችን ለማድረግ፣ ሰነድን ለማጋራት የሚያስችል ሲሆን መልዕክቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ (encrypted) እንዲተላለፉ ያስችላል፡፡
- የመልቲሚዲያ መልዕክት አገልግሎት/ Multimedia Messaging Service(MMS) ፡- በተመሳሳይ ሁኔታ ኩባንያችን ተጨማሪ አዳዲስ ይዘቶችን (features) ያካተተ የመልቲሚዲያ መልዕክት አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል፡፡ አገልግሎቱ (MMS) የቪዲዮ እና ኦዲዮ/ድምጽ ፋይሎችን ለመላክ እና ለመቀበል፣ በርካታ መልዕክቶችን ለተለያዩ ተቀባዮች በአንድ ጊዜ ለመላክ እንዲሁም እስከ 1600 ፊደላት/character/ የሚደርስ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ/ለመላክ እና የተላከው መልዕክት መቼ እንደደረሰና እንደተነበበ ለማወቅ የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡
- የድምጽ መልዕክት አገልግሎት /Voce Mail Services (VMS) ደግሞ ደንበኞች ከኔትወርክ ሽፋን ውጭ ሲሆኑ፣ ስልካቸው በሌላ ጥሪ ሲያዝ፣ ሲጠፋ (switch off) ወይም በተለያየ ምክንያት ጥሪ መቀበል በማይችሉበት ጊዜ ደዋዮች በድምጽ መልዕክት የተቀረጸ መልዕክት እንዲያስቀምጡ በማድረግ፣ በተመቻቸው ጊዜ የተቀመጠላቸውን የድምጽ መልዕክት እንዲያዳምጡ የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡
በመጨረሻም ኩባንያችን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት በተለይም በዛሬው ዕለት ተግባራዊ ያደረግነውን የቮልቲኢ መሠረተ ልማት ሥራ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እንድንችል እገዛቸው ላልተለየን የቴሌኮም ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ ስማርት ቀፎ አምራቾች፣ የኩባንያችን ቤተሰቦች እና የቢዝነስ አጋሮቻችን ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የቮልቲኢ አገልግሎትን ለማስጠቀም የሚያስችሉ ስልኮች ዝርዝር ለመመልከት እዚህ ይጫኑ
ታህሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.
ኢትዮ ቴሌኮም