የተለመዱ የቴሌኮም ማጭበርበር አይነቶች

1. ማህበራዊ ኢንጂነሪንግ

ይህ ዘዴ አጭበርባሪዎች ያልሆኑትን ማንነት በመላበስ (ተቋማትን ወይም ሌሎች ግለሰቦችን በመምሰል) ሚስጥራዊ ወይም የግል መረጃዎችን እንዲሰጧቸው የሚያሳምኑበት ዘዴ ነው፡፡ አጭበርባሪዎች በአጭር የፅሁፍ መልዕክት፣ በኢሜይል፣ በማህበራዊ ገፆች መልዕክት በመላክ ወይም የስልክ ጥሪ በማድረግ የማጭበርበር ድርጊቱን ይፈፅማሉ፡፡

መሰረታዊ የማህበራዊ ኢንጂነሪንግ ማጭመርበሪያ መንገዶች

ሀ. በአካል

    • በቡድን ውይይት የሀሳብ ልውውጥ ወቅት የሚደረግ ጥቃት
    • የሰውነት እንቅስቃሴን በማስመሰል (በሚገለጹ ሀሳቦች)

   ለ. በስልክ

    • ድጋፍ (እርዳታ) እንደፈለጉ በማስመሰል እና በመደወል የአየር ሰዓት ወይም ገንዘብ እንዲልኩ መጠየቅ
    • ከታወቀ ድርጅት የተደወለ በማስመሰል እና የበጎአድራጎት ብር እንዲለግሱ ማግባባት
    • መልሰው እንዲደውሉ መለያ ቁጥርን ወይም ግብይትን እንዲያረጋግጡ መጠየቅ

 ሐ. ፊሺንግ

    • በኢሜይል ወይም በአጭር ቁጥር ሐሰተኛ ማስፈንጠሪያ በመላክ
    • ትክክለኛ ያልሆነ ድረ-ገፅ/ማህበራዊ ሚዲያ በመክፈት እና ትክክለኛ አርማ በመጠቀም ወይም በማስመሰል መረጃ መጠየቅ

 

2. አካውንትን መጥለፍ

አጭበርባሪዎች በሞባይል ኦፕሬተር ውስጥ ያለን ክፍት አካውንት በመጥለፍ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙበት ዘዴ ነው፡፡ የአጭበርባሪዎቹ ዋና አላማ አካውንቱን በመጠቀም ያለምንም ፈቃድ የሚፈልጉትን ጥቃት ማሳካት ነው፡፡

 የአካውንት መጥለፍ ማጭበርበር እንዴት ይፈጸማል?

  • የተሰረቁ ሲም ካርዶችን በመጠቀም
  • የደንበኞችን አካውንት ከእውቅናቸው ውጪ መጠቀም የሚያስችል አጋጣሚ ሲያገኙ

3. ሲም ካርድን በመተካት (SIM SWAP) የሚፈጸም ማጭበርበር

አጭበርባሪዎች የደንበኞች አገልግሎት የአሰራር ሂደትን በማታለል እና የደንበኞችን ሲም ካርድ ምትክ በመውሰድ በአጭር ጽሁፍ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመጥለፍ የሚከናወን የማጭበርበር አይነት ነው።

የማጭበርበር ድርጊቱ ለምን ይፈጸማል?

ይህ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጸማ፣ በፅሁፍ መልዕክት የሚላክን የደንበኞች የአካውንት የይለፍ ቁጥር ደካማ አያያዝ (Weak Password Handling) በመጠቀም አጭበርባሪው የባንክ ማጭበርበርን ለመፈጸም፣ የሞባይል ገንዘብ ሂሳብን ለመውሰድ እና ሌሎች የሶስተኛ ወገን OTT አካውንቶችን ለመቆጣጠር ይከናወናል፡፡

4. ዋንጊሪ ማጭበርበር

በኮምፒዉተር የታገዘ እና ብዙ የሞባይል ስልክ ቁጥሮች ላይ በዘፈቀደ (random) በመደወል የሚፈጸም ማጭበርበር ነው።

የማጭበርበር ድርጊቱ እንዴት ይፈጸማል?

አጭበርባሪዎች በማንኛውም የስልክ ቁጥር ላይ (randomly) ፈጣን ጥሪ በማድረግ እና ጥሪው ሳይነሳ በቶሎ በመዝጋት ወይም መልዕክት በመላክ የተደወለለት ግለሰብ ጥሪውን ሲመልስ ለከፍተኛ ክፍያዎች የሚዳርግ የማጭበርበር ድርጊት ነው፡፡

5. የሞባይል ገንዘብ (ቴሌብር) ማጭበርበር

የቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መምጣትን ተከትሎ በቅርብ ጊዜ የተከሰተ የማጭበርበር አይነት ሲሆን፣ አላማውም የቴሌብር አካውንት ላይ ያለ ገንዘብን መውሰድ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡  

አጭበርባሪዎች እንዴት ጥቃት ያደርሳሉ?

    • አጭበርባሪዎች የስልክ ጥሪ ወይም መልእክት ወደ ደንበኞች በመደወል እና በመላክ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት
    • ከሚታወቀ ድርጅት እንደደወሉ በማስመሰል
    • የአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል በመጠየቅ
    • ደንበኞችን በማታለል ገንዘብ እንዲልኩ በማድረግ

6. የክፍያ ማጭበርበር

የተሰረቀ የቴሌ ብር አካውንት ወይም ያልተፈቀደ የክፍያ መረጃን በመጠቀም ግብይት የማከናውን ድርጊት ነው.

የክፍያ ማጭበርበር መቼ ይከሰታል?

አንድ ሰው የሌላውን ሰው የክፍያ መረጃ (ለምሳሌ ቴሌብር ወይም የባንክ ሂሳብ) በመስረቅ

ያልተፈቀደ ግብይት ወይም ግዢ ለመፈጸም የሚደረግ ማጭበርበር ነው፡፡

የማጭበርበር ድርጊቱ እንዴት ይፈጸማል?

    • የሐሰት የደንበኞች መረጃን በመፍጠር እና ቴሌብር አካውንት በመክፈት
    • የተሳሳተ የገንዘብ ክፍያ እና መረጃ በማዘጋጀት
    • ሐሰተኛ የባለቤትነት መብቶችን በመጠቀም