ከቴሌኮም ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የተወሰደ እርምጃን በተመለከተ ከኢትዮ ቴሌኮም የተሰጠ መግለጫ”
ለህገወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት ሲውሉ የነበሩ በአዲስ አበባ ከተማ 34፣ በጅማ ዞን 32 ሲም ቦክሶች እና ሌሎች ለዚሁ ተግባር የዋሉ መሳሪያዎች እንዲሁም በዚህ ህገወጥ ተግባር የተሳተፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ለህገወጥ ዓላማ የዋሉ መሳሪያዎችና ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተደረገው ጥረት የደህንነት፣ የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት፣ የፍትህ አካላት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኃላፊዎች ፣ የጅማ ዞን እና ከተማ የመንግስት ኃላፊዎች ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መ/ቤት የመረጃ ደህንነት፣ የደቡብ ምዕራብ የኢትዮ ቴሌኮም አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በንቃት እና በቅንጅት ስራውን አከናውነዋል፡፡
በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸመው የማጭበርበር ድርጊት በቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ባሻገር፣ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት እና በሀገር ደህንነት ላይ ስጋት የሚፈጥር ህገወጥ ተግባር ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የዓለም አቀፍ አገልግሎትን ለማሻሻል እንዲሁም የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከል ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ የቢዝነስ ስትራቴጂ በመንደፍ እንዲሁም የቴክኒክ መፍትሔዎችን በመተግበር ላይ ሲሆን የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶች ከሚያደርሱት የኢኮኖሚ ኪሳራ በተጨማሪ በሀገር ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ በመገንዘብ ህብረተሰቡ በቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት ሲገኙ ለተቋሙ፣ ለጸጥታና ለህግ አስከባሪ አካላት ጥቆማውን በማቅረብ ህገወጦችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ጥሪያችንን እያስተላለፍን በዚህ ህገወጦችን እና ህገወጥ ድርጊቶችን ለማስቆም በተደረገው ጥረት ውስጥ ለተሳተፉ አካላት ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡