ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በዘረጋቸው መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማቶች አማካኝነት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የቴሌኮም ደንበኞቹ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ደረጃ የኃይል ፍጆታን የሚቀንስ፣ በቀላሉ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችልና ፈጣን የሲስተም ተከላ ለማድረግ የሚያስችለውን ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል (Modular Data Center) በዛሬው ዕለት ሥራ አስጀምሯል፡፡
ኩባንያው የሚጠቀምበት የዳታ ማዕከል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ሥራዎች ሲሠሩ የቆየ ሲሆን እነዚህ ሥራዎች በመጠናቀቃቸው ቀደም ሲል የነበረውን የመረጃ ማዕከል ለመተካት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ (Standard) የመረጃ ማዕከል ተገንብቶ ለምረቃ በቅቷል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶችን መስጠት ለሚፈልጉ ድርጅቶች በአጭር ጊዜ የመረጃ ቋቱን በመጋራት (data center collocation) ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችላቸው ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ችግርን ለመቅረፍ ደግሞ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ጀኔሬተሮች እና የኃይል ማጠራቀሚያ ባትሪዎች እንዲሁም የማይቆራረጥ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ሌሎች መሣሪያዎች ተገጥመውለታል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ ማዕከሉ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችት እና ስርጭት ዓለም አቀፍ ጥራቱንና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ አገልግለት የሚሰጥ የመረጃ ማዕከል በመሆኑ ለተቋማት የአገልግለት ጥራት እና አስተማማኝነት ወሳኝ ነው፡፡
ይህ በዛሬው ዕለት የተመረቀው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ወጪ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቆጣቢ የሆነ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሲስተሞች ላይ የኔትዎርክ ኮኔክሽንም ይሁን ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ቢያጋጥሙ ፈጣን ፍተሻና ጥገና ለማከናወን የሚያስችል (quick incident detection and maintenance) ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ ማዕከል ነው፡፡
ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ ኃይልን የሚቆጥብ የኤሌክትሪክ ሲስተም፣ የማቀዝቀዣ ሲስተምና የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙለት ሲሆን በተጨማሪም ዘመናዊ የሆነ የኔትዎርክና የፋይበር ኬብል ማቀፊያዎች እና ኮምፓርትመንቶች ያሉት ነው፡፡
ማዕከሉ ኩባንያው አገልግሎት ለሚሰጥባቸው ለሁሉም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅና የኔትዎርክ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የMobile Money system እና የNext Generation Business Support System ዕቃዎች ተተክለውበታል፡፡
ከዚህም ባሻገር የመረጃ ማዕከሉ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችል በመሆኑ ወደፊት የተጨማሪ እሴት አገልግሎት (Value Added Service)፣ የጥሪ ማዕከል (Contact Center) እና የኦፕሬሽን ሳፖርት (OSS) ሲስተሞችን እንዲያካትት የሚደረግ ሲሆን ፕሮጀክቱ የራሱ የሆነ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ያለው ነው።