ኩባንያችን ከፍተኛ የዳታ አጠቃቀም በሚታይባቸው 103 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎትን ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በሚገኙ 2 ከተሞች ማለትም ጎንደር እና ደብረታቦር የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አጠናቆ አገልግሎቱን ማስጀመር ችሏል።
የ4ጂ አገልግሎት የላቀ ፍጥነትና ባንድዊድዝ እንዲሁም አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ደንበኞቻችን አገልግሎታቸውን ዲጂታይዝ ለማድረግ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያስችላቸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን ባደረጋቸው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት ኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራዎች 65 ከተሞችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን በቀጣይነትም ኩባንያችን በተመሳሳይ ሁኔታ የዳታ ትራፊክ እድገትና ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ በዕቅድ ይዞ እያከናወናቸው ያሉ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት የማስፋፊያ ሥራዎችን በማጠናቀቅ በተለያዩ የክልል ከተሞች አገልግሎቱን በቅርቡ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዚህ አጋጣሚ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት በተስፋፋባቸው ከተሞች የምትገኙ ደንበኞች በአቅራቢያችሁ በሚገኝ የኩባንያችን የሽያጭ ማዕከል የ3ጂ ሲም ካርዳችሁን ወደ 4ጂ በነፃ በማሳደግ 4ጂ ኤል.ቲ.ኢ መጠቀም በሚያስችል የሞባይል ቀፎ፣ ታብሌት ወይም ዶንግል አማካኝነት እጅግ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እንድትጠቀሙ ግብዣችንን እናቀርባለን።
በተጨማሪም የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሣሪያ (smart phone) እና የይዘት (content) አቅራቢዎች በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብና ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እና አሁን የተዘረጋውን ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የሞባይል ኔትወርክ በስፋት ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችና ይዘቶችን ለህብረተሰቡ በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የበኩላችሁን አስተዋጽዖ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።