ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የገነባቸውንና ጎብኚዎች በእንጦጦ ፓርክ የዳታ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸውን ስማርት ማማ (smart pole) የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ስማርት ማማው የጎብኚዎችን ፍሰት መሰረት በማድረግ የፓርኩን ተፈጥሯዊ ገጽታውን በጠበቀ እና ለዕይታ ማራኪ በሆነ ዲዛይን የተተከለ ሲሆን በቀጣይም በፓርኩ ውስጥ ለሚከናወነው የ5ኛው ትውልድ (5G technology) ኔትወርክ ዝርጋታ ዝግጁ እንዲሆን መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በቀጣይ ኢኮ ቱሪዝም በሚካሄድባቸው የተለዩ ስፍራዎች ጋር የሚመሳሰሉ የካሞፍላጅ ማማዎች (Camouflage Towers) እንደሚተከሉ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም በእንጦጦ ፓርክ እንደ ማሳያ ተደርጎ የቀረበው ይህ ዘመኑ ያፈራው ቴክኖሎጂ በቀጣይም የዘመናዊ ከተሞችን (Smart City) አስቻይ መሠረተ ልማቶችን ማለትም ለቴሌኮም አገልግሎት፣ ለመንገድ መብራት፣ ለአየር ንብረት ልኬት፣ ለትራፊክ ማኔጅመንት፣ ለደኅንነት ካሜራ፣ ለማስታወቂያ ስክሪን እና አማራጭ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያን በአንድ ላይ ማቀናጅት የሚያስችሉ ስማርት ማማዎችን ከተለያዩ የማንግስት እና የግል ተቋማት ጋር በመተባበር የሚተክል መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም